Ethiopia: የወያኔ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመውደቂያው ሰበር ዜና ነው

የወያኔ መንግስት ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያደረበት ፍርሃት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንና እንደሰደድ የተያያዘው የህዝባዊ እምቢተኝነት ድል የነሳውና ያንበረከከው የመሆኑ ምልክት ነው። ላለፉት 25 ዓመታት በወታደር ጠመንጃና በደህንነት ታፍኖና ተወጥሮ የኖረህዝብ በጊዜያዊ አዋጅ ሥር ነውና ለምን ይህን አዋጅ ማወጅ እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም። የበለጠ ያለ ገደብ የመግደያና የማሰር፣ ሰላማዊውን ሕዝብ የማንገላታት አድማሱን አስፍቶ ለማንም ስብዕናና ሕሊና ላለው የማይዋጥ የመጨፍጨፊያ ፈቃድ አለን ለማለት ካልሆነ በስተቀር።

ከትቂት ዓመታት በፊት የወጣው የፀረ ሽብሩ አዋጅ የሃገሪቱን ሕገመንግስት ገርስሶ፣ የህዝብ መብት ነጥቆ፣ አስተዳደሩን በወታደር፣ በሰላዮችና በካድሬዎች ሥር የጣለው መሆኑን ወያኔ ዘንግቶት አይመስለንም። የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብና የእምነት ነጻነት ህዝቡከተነፈገ ዓመታት አስቆጥሯል። የወያኔ ገዳዮች፣ አሳሪዎችና ዘራፊዎች አይከሰሱም አይገሰሱም። ስለሆነም የፀረ ሽብር አዋጁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነበር ለማለት ነው።

በአገሪቱ ሕግ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ ያለበት አገር በውጭ ጠላት ሲወረር፤ የተፈጥሮ አደጋ ሲፈጠርና ደህንነትን የሚያናጋ የወረርሽኝ ደዌ ሲደርስ ነው። አዋጅ የሚሆነውም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደንግጎና አልፎ በ2/3 ድምፅ የተወካዮች ምክር ቤት ሲያፀድቀው ነው። ወያኔዎች ሕግ አውጭም አስፈፃሚም ናቸውና በፓርላማ ሣይፀድቅ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያወጁት። ማን ቢጠይቃቸው?

በአሁኑ ሰዓት አገርን ባስመረረው የአግአዚ ጦሩና እንደ ተፈጥሮ አደጋ የደሀውን ቤት በሚያወድመው አፍራሽ ግብረ ሃይሉ አማካይነት ሰላማዊውን ሕዝብ በማሸበርና በማስጨነቅ ሕዝቡን በሽታ ላይ የጣለው ራሱ የወያኔ ሥራዓት ነው። ስለዚህ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማወጅየነበረበት በሕዝቡ ላይ ሳይሆን በራሱ ላይ ነበር።

ይህ የህዝብ ማጥቂያ አዋጅ የህዝቡ ቁጣና ቁርጠኝነት እንዲያይልና እንዲገነፍል ከማድረጉም በላይ እንደ ባህር ሞገድ የወያኔን የተንኮል ጀልባናባለስልጣናቱን አረፋ እያስደፈቀ የሚያሰጥም እንደሚሆን ጥርጥር የለንም።

መታወቅ ያለበት ወያኔ የመጨረሻውን ሲቃ እስከሚተነፍስ ድረስ ከመቸውም የከፋ አደጋ ማድረሱ አይቀርምና ወገኖቻችን በአንድነት፣ በብልህነትና በጀግንነት በጋራ ለመመከት መዘጋጀት አለባቸው። ወያኔዎች ስልጣን ያሰከራቸውና በተዘረፈ ገንዘብ ያበዱና ራስ ወዳዶችናቸውና አጥፍቶ መጥፋት  የሚሳናቸው አይደሉም።

ህዝብም እርስ በእርሱ እንዲጠፋፋ ባላቸው ፕላን መሰረት የወያኔ ካድሬዎችና የደህንነት ሰዎች ባቀነባበሩት ሴራ በደቡብ ክልል በጌድዮ ዞን በዲላ ወረዳ በወያኔ በተወናበዱ ጥቂት የጌድዮ ተወላጆች በአማራና በጉራጌዎች ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ በመክፈታቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶችና መኖሪያ ቤቶች የንግድ ተቋሞች እንዲቃጠሉ ተደርጓል። ይህ ዓይነቱ ወንጀል በሌላም አካባቢዎች እንዳይደገም ሕዝቡ ነቅቶ መጠበቅ አለበት።

በቂሊንጦ እስር ቤት ወገኖቻችንን በእሳት የፈጁበት ሀዘን ከሰው ልብ ሣይጠፋ በዝዋይ እስር ቤት የሚፈልጓቸውን እስረኞች ለመግደልበማሴር የወያኔ ካድሬዎች ባስነሱት እሳት 11 እስረኞች እንደተገደሉ ይፋ ሆኗል።

ምዕራባውያን አገሮች የህዝቡ ደም ለዓመታት በግፍ ሲፈስ ጉዳዩ አሳስቦናል ከማለት ባለፈ እልቂቱን የሚያስቆም እርምጃካለመውሰዳቸውም በላይ ይህን የወንበዴ ሥራዓት መደጎማቸውን እንደቀጠሉ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀም በኋላ አሁንም ዓይኔን ግንባር ያድርገው ምንም አላየሁም የሚሉ ይመስላሉ። ያለፈው ልምዳችን እንደሚያሳየን ከሆነ ግን ከነሱ ብዙም መጠበቅ እንደለለብንነው።

እነሱ በሚለግሱት ገንዘብ በተሸመተ ጥይት ሕዝባችን እንደ ቅጠል ሲረግፍ በእሳት ሲፈጁትና ገደል ሲያስገቡት ምዕራባውያን አድም እርምጃ አልወሰዱም። በዚህም ድርጊት ከእኛ ህይወት የራሳቸው ጥቅም እንደሚያመዝን እየነገሩን ነው። ስለሆነም መገንዘብና ማመን ያለብን የወያኔሥራዓት  እየፈፀመ ካለው ድብደባ፣ ግድያ፣ እሥራትና ሽብር የፈጣሪ እርዳታ ተጨምሮበት ሕዝባችንን መታደግ የምንችለው እኛና እኛ ብቻመሆናችንን ነው።

የወያኔን ሰው በላ ሥራዓት ከሥሩ ነቅንቆ ያንገዳገደውና ፍርሃትን በ25 ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ  የሰበረው የሙስሊሙ አይበገሬፊልሚያ፣ የኦሮሞው ጀግንነትና የአማራው ቆራጥነት በድምሩ የወያኔ ሥራዓት ተንኮታኩቶ ግብዓተ መሬቱ በቅርቡ የሚፈፀም መሆኑንአመላካቾች ናቸው።

መሣሪያ ታጠቃችሁ ይህን ሥርዓት በማገልገል ላይ የምትገኙ ወገኖቻችን በተለይ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኋላ ከራሳችሁ ጋር መክራችሁ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን መግደል አቁማችሁ ከወያኔ ካምፕ ውጡና ወደ ሕዝብ ጎራ እንድትቀላቀሉ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን።

በአገርና በውጭ ያለችሁ የትግራይ ወገኖቻችንም እናንተን የማይወክሉና ሊወክሏችሁም የማይችሉ ጥቂት ወንጀለኞች በእናንተ ስም በኦሮሞ፣ በአማራውና በኮንሶ ሕዝቦች ላይ የሚያደርሱትን የዘር ማጥፋት ዘመቻ በማውገዝ እየደማ፣ እየቆሰለና እየሞተ ካለው ወገናችሁ ጎን ተሰልፋችሁ የወያኔን ስራዓት በቁርጠኝነት ታገሉ።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ሕብረት የወያኔ ሥራዓት የአገሪቱን ሕገ መንግስት በመጣስና የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም በአስቸኳይ አዋጅ ከለላ ሥር ለራሱ የሰጠውን ሕዝብን የመፍጀት የምስክር ወረቀት ወይም ፈቃድ በጽኑ ያወግዛል።

የወያኔ ሥራዓት ያስተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመውደቂያው ሰበር ዜና ነውና አገዛዙ ሙሉ ለሙሉ እስኪያከትም ድረስ መራራውን ትግል በጋራ እንድንቀጥል ጥሪያችንን እናስተላልፋላን።
ትግላችን  በአላህ  ፈቃድ  እስከ  ድል  ደጃፍ  ይቀጥላል!

ምንጊዜም  ድል  የሕዝብ  ነው!

አላሁ አክበር!!!

የኢትዮጵያ  ሙስሊሞች  ሰላማዊ  ንቅናቄ  ደጋፊዎች  ሕብረት